መግቢያ

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂና የከተማ ልማት ፖሊሲ ላይ ተመስርቶ የራሱ ፕሮግራምና ዝርዝር የድጋፍ ፓኬጅ ተዘጋጅቶለት ላለፉት አመታት በኢንተርፕራይዞች ልማት አበረታች ውጤት አስገኝቷል፡፡ የድጋፍ ፓኬጁም በተመረጡ ዕድገት ተኮር ዘርፎች ላይ በማተኮር ለኢንተርፕራይዞች ድጋፍ መስጠት አስችሏል፡፡ በዚህም መሠረት በተለያዩ የምርትና የአገልግሎት ሙያዎች ለተሠማሩ በርካታ ኢንተርፕራይዞች አስፈላጊው የማደራጀት፤ የማሰልጠን፣ የፋይናንስና እንዲሁም የማምረቻና የመሸጫ ቦታ አቅርቦቶች እና የገበያ ትስስር ድጋፎች እንዲያገኙ በማድረግ ሰፊ የስራ ዕድል እንዲፈጠርና ለድህነት ቅነሳ ፕሮግራሙ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

ሆኖም የተሰጡት ድጋፎች ኢንተርፕራይዞቹ በየዕድገት ደረጃቸው ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሄ በመስጠት ረገድ ውሱንነት ታይቶባቸዋል፡፡ በዚሁ መሰረት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ የድጋፍ ማዕቀፍና የአፈፃፀም ስልቶች ሰነድን መሠረት በማድረግ ኢንተርፕራይዞችን እንደየዕድገት ደረጃቸው በመክፈል የተቀመጡ ሲሆን፤ እነርሱም ምስረታ ወይም ጀማሪ /Start-up/ ደረጃ፣ ታዳጊ ወይም መስፋፋት /Growth/ ደረጃ፣ እና መብቃት /Maturity/ ደረጃ ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህንን የኢንተርፕራይዞች የዕድገት ደረጃ ክፍፍል መሠረት በማድረግ ኢንተርፕራይዞቹ በየዕድገት ደረጃቸው የሚያስፈልጓቸው ድጋፎች መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በዚሁ መሰረት የኢንተርፕራይዞች የዕድገት ደረጀ ሽግግር መስፈርቶች፣ በመስፈርቶቹ መሰረት በሚኖሩ የኢንተርፕራይዝ የዕድገት ደረጃዎች የሚሰጡ የድጋፍ ማዕቀፎች እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ትርጓሜ

  1. ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ማለት የኢንተርፕራይዙን ባለቤት፤ የቤተሰብ አባላትና ተቀጣሪ ሰራተኞች ጨምሮ እስከ አምስት ሰዎች ቀጥሮ የሚያሰማራና የጠቅላላ ካፒታሉ መጠን ህንፃን ሳይጨምር በአገልግሎት ዘርፍ ከብር 50000 (ሃምሳ ሺ) ወይም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከብር 100000 (አንድ መቶ ሺ) ያልበለጠ ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡
  2. አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ማለት የኢንተርፕራይዙን ባለቤት፤ የቤተሰብ አባላትና ተቀጣሪ ሰራተኞችን ጨምሮ ከስድስት እስከ ሰላሳ ሰዎች የሚያሰማራና የጠቅላላ ካፒታሉ መጠን ህንፃን ሳይጨምር በአገልግሎት ዘርፍ ከብር 50001 (ሃምሳ ሺህ አንድ) እስከ 500000 (አምስት መቶ ሺህ) ወይም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከብር 100001 (አንድ መቶ ሺህ አንድ) እስከ 1500000 (አንድ ሚልዮን አምስት መቶ ሺ) ያልበለጠ ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡
  3. የኢንተርፕራይዝ ደረጃ ሽግግር ማለት አንድ ኢንተርፕራይዝ ባለቤት የዕድገት ደረጃ የሚሰጠውን ድጋፍ ተጠቅሞ በገበያ ላይ በዋጋ፣ በጥራትና በአቅርቦት ተወዳዳሪ ሆኖ የቀጣይ የዕድገት ደረጃ የሽግግር መስፈርቶቹን በማሟላት መሻገር ሲችል ነው፡፡
  4. የምሥረታ/ጀማሪ ደረጃ ማለት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመመሥረት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እና ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት በየደረጃው የሚጠበቅባቸው ትምህርት በማጠናቀቅና በህብረት ስራ ማህበር፤ በሽርክና ማህበር እና በግለሰብ በሕግ አግባብ ተደራጅተው የራሳቸውን ቁጠባና ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ብድር በመውሰድ ወደ ሥራ የገቡትን የሚያካትት ነው፡፡ የምሥረታ /ጀማሪ ደረጃ ኢንተርፕራይዝ ሕጋዊ አቋም ይዞ የማምረትና አገልግሎት የመስጠት ተግባር የሚጀምርበት ነው፡፡
  5. "የታዳጊ/መስፋፋት ደረጃ" ማለት አንድ ኢንተርፕራይዝ የሚሰጠውን ድጋፍ ተጠቅሞ በገበያ ላይ በዋጋ፣ በጥራትና በአቅርቦት ተወዳደሪ ሲሆንና ትርፋማነቱ በቀጣይነት ሲረጋገጥ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ያለ ኢንተርፕራይዝ በምሥረታ ደረጃ ከነበረው ቀጥሮ የሚያሠራው የሰው ኃይል ቁጥርና የጠቅላላ ሀብት መጠን ዕድገት ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም ኢንተርፕራይዙ የሂሳብ አያያዝ ሥርዓት የሚጠቀም ይሆናል፡፡
  6. "የመብቃት ደረጃ" ማለት አንድ ኢንተርፕራይዝ የሚሰጠውን ድጋፍ ተጠቅሞ በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪና ትርፋማ ሆኖ የገበያ ድርሻውን ለማሳደግ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት በሥራ ላይ ካዋለና ለዘርፉ የተቀመጠውን ትርጓሜ መሥፈርት ሲያሟላና ወደ ታዳጊ መካከለኛ ሲሸጋገር ወይንም በአለበት ደረጃ ጥቃቅን ወይንም አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ በመሆን በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪና ትርፋማ ሆኖ የሚቀጥል ሲሆን ነው፡፡
  7. "ታዳጊ መካከለኛ ደረጃ" ማለት ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተቀመጠውን የሰው ሃይልና ጠቅላላ ሃብት መጠን የመብቃት የዕድገት ደረጃ በማለፍ ወደ ኩባንያ ደረጃ የተሸጋገረ የኢንተርፕራይዝ የዕድገት ደረጃ ማለት ነው፡፡
  8. "ቋሚ የሥራ ዕድል" ማለት በማናቸውም ኢንተርፕራይዝ ውስጥ የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ የሙሉ ጊዜ ተቀጣሪ በመሆን በፔይሮል ክፍያ በማግኘት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ማለት ነው፡፡
  9. "ጊዜያዊ የሥራ ዕድል" ማለት በማናቸውም ኢንተርፕራይዝ ውስጥ ከአንድ ዓመት ላነሰ ጊዜ ክፍያ ለማግኘት ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ማለት ነው፡፡
  10. "ኢንተርፕረነርሽፕ" ማለት አንድ ኢንተርፕራይዝ በተሰማራበት ዘርፍ ገበያ ለማግኘት የሕብረተሰቡን የምርትና የአገልግሎት አቅርቦት ፍላጎት በመለየት እንዲሁም ተወዳዳሪዎችንና የገበያ ድርሻቸውን በመለየት ስለ አዋጭነቱ መተማመን ደረጃ ሲደረስ ምርትና አገልግሎት ሥራ የመሰማራት ክህሎት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
  11. " የገበያ ትስስር" ማለት ለአንድ ኢንተርፕራይዝ የገበያ ዕድል ለመፍጠር ከመንግስት ተቋማት ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች በሀገር ውስጥና ውጪ ከሚገኙ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር በግብዓት፣ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት በጎንዮሽና በተዋረድ ግንኙነት የሚፈጠር የግብይት ወይም የሥራ ትስስር ነው፡፡
  12. "ጠቅላላ ሀብት" ማለት የአንድ ኢንተርፕራይዝ የተከፈለ እና በብድር የተገኘ ሀብት ነው፡፡
  13. "የተጣራ ካፒታል" ማለት የአንድ ኢንተርፕራይዝ ጠቅላላ ሀብት ሲቀነስ ዕዳ ማለት ነው፡፡
  14. "የምርት ወይም የአገልግሎት ማስተዋወቂያ ዘዴዎች" ማለት ምርትን ወይም አገልግሎትን ለማስተዋወቅ የመገናኛ ብዙሃን፣ ንግድ ትርዒትና ባዛር፣ ብሮሽር፣ ቢዝነስ ካርድ፣ ቋሚ የማስታወቂያ ሰሌዳ፣ ማሸጊያ እና የመሳሰሉትን የካትታል፡፡

የኢንተርፕራይዞች የዕድገት ደረጃ አወሳሰንና ሽግግር

  1. አዲስ ለሚደራጁ የኢንተርፕራይዞች የዕድገት ደረጃ አሰጣጥ
    በስትራቴጂው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ህጋዊ በሆነአደረጃጀት ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉ ኢንተርፕራይዞች የያዙትን የሰው ኃይልና የካፒታል መጠን መሰረት በማድረግ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዓይነት ተለይተው ጀማሪ የዕድገት ደረጃ እንድሰጣቸው ይደረጋል፡፡
  2. ለነባር ኢንተርፕራይዞች የእድገት ደረጃ እድሳት የቆይታ ጊዜ አንድ ኢንተርፕራይዝ የእድገት ደረጃ ማደስ የሚችለው በዓመት አንዴ (1)ጊዜ ብቻ ይሆናል፡፡
  3. ለኢንተርፕራይዞች የሚሰጥ የእድገት ደረጃ እርከን አንድ ኢንተርፕራይዝ ለደረጃው የጠቀመጠ መስፈርት አሟልተው ከተገኘ የእድገት ደረጃ እርከን ሳይጠብቅ መሸጋገር ይችላል፡፡
  4. ከማንኛውም የእድገት ደረጃ ወደ ታዳጊ መካከለኛ ለተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች የእድገት ደረጃ ሽግግር የሚደረገው በዓመቱ መጨረሻ ብቻ ስሆን ኢንተርፕራይዞቹ የያዙት ሰርተፊኬት ጊዜው ያበቃ ከሆነ የያዙት የእድገት ደረጃ እንድታደስላቸው ይደረጋል፡፡
  5. የእድገት ደረጃ የሚሰጣቸው በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ብቻ ይሆናል፡፡
    የእድገት ደረጃ የማይሰጣቸው የስራ ዘርፎች
    ከዚህ በታች የተዘረዘሩ የስራ ዘርፎች አንቀሳቃሾች መነሻ ከፒታል የሚያፈሩበት የስራ ዘርፍ በመሆኑ የእድገት ደረጃ አይሰጣቸውም፡፡
    1. ኮብልስቶን ስራ (መፍለጥ፤ መጥረብ፤ ማንጠፍ ስራ) የእድገት ደረጃ የማይሰጣቸው ዘርፎች ናቸው፡፡
    2. የታክስ ተራ አስከባሪ፤
    3. የጥበቃ አገልግሎት፤
    4. ደረቅና ፋሳሽ ቆሻሻ መሰብሰብ፤
    5. ፓርኪንግ፤
    6. የመንገድ ጽዳት ስራዎች፤
    7. የውሃና መብራት ቢል፤
    8. የኪራይ ቤቶችን የወራሃዊ ኪራይ የመሰብሰብ ስራዎችና
    9. ሌሎች ዘርፎች ማለትም አንቀሳቃሾች መነሻ ከፒታል የሚያፈሩበት የስራ ዘርፎችየእድገት ደረጃ አይሰጣቸውም፡፡. ”
የኢንተርፕራይዞች የዕድገት ደረጃ አወሳሰንና ሽግግር መስፈርቶች

ከጀማሪ/ምስረታ ወደ ታዳጊ የሚሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች ሊያሟሉዋቸው የሚገቡ ዝርዝር መስፈርቶች

  1. በሥራ ዕድል ፈጠራ
    ሀ) በኢንዱስትሪም ሆነ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ የፈጠረው ቋሚ የሥራ ዕድል የኢንተርፕራይዝ አባላቱን ጨምሮ እስከ 5 ሰዎች መሆን ይኖርበታል፡፡
    ለ) በኢንዱስትሪም ሆነ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የፈጠረው ቋሚ የሥራ ዕድል የኢንተርፕራይዝ አባላቱን ጨምሮ ከ6 እስከ 10 ሰዎች መሆን ይኖርበታል፡፡
    ሐ) በኢንዱስትሪም ሆነ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ አንሰተኛ ኢንተርፕራይዝ በዓመት ውስጥ በጊዜያዊነት የፈጠረው የሥራ ዕድል ከ6 እስከ 1ዐ ሰዎች መሆን ይኖርበታል፡፡
  2. በሃብት መጠን
    2.1 በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ
    ሀ) ጠቅላላ የሃብት መጠን የተጣራ ሀብት እና ዕዳን የሚያካትት ሆኖ ለጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ከብር 50000 እስከ 75000 መሆን ይኖርበታል፡፡
    ለ) ጠቅላላ የሃብት መጠን የተጣራ ሀብት እና ዕዳን የሚያካትት ሆኖ ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ከብር 100000 እስከ 500000 መሆን ይኖርበታል፡፡
    ሐ) ኢንተርፕራይዙ በብድር ካገኘው ገንዘብ ለቋሚ ንብረት ያዋለው 50 እና በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
    2.2 በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ፤
    ሀ) ጠቅላላ የሃብት መጠን የተጣራ ሀብት እና ዕዳን የሚያካትት ሆኖ ለጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ እስከ ብር 40000 መሆን ይኖርበታል፡፡
    ለ) ጠቅላላ የሀብት መጠን የተጣራ ሀብት እና ዕዳን የሚያካትት ሆኖ ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ከብር 50001 አስከ ብር 200000 መሆን ይኖርበታል፡፡
    ሐ) ኢንተርፕራይዙ በብድር ካገኘው ገንዘብ ለቋሚ ንብረት ያዋለው 20 እና በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
  3. በትርፋማነት
    3.1 በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች
    ሀ) ተመጣጣኝ የትርፍ መጠን በማግኘት በተከታታይ ዓመታት ያስመዘገበ መሆን ይኖርበታል፡፡
    ለ) ከተገኘው ትርፍ ሥራውን ለማስፋፋት ያዋለው ኢንቨስትመንት እና ወይም የቁጠባ መጠን ከተጣራ ሀብት ከ15 በላይ መሆን ይኖርበታል
    3.2 በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች
    ሀ) ተመጣጣኝ የትርፍ መጠን በማግኘት ተከታታይ ዓመታት ያስመዘገበ መሆን ይኖርበታል፡፡
    ለ) ከተገኘው ትርፍ ሥራውን ለማስፋፋት ያዋለው ኢንቨስትመንት እና ወይም የቁጠባ መጠን ከተጣራ ሃብት ከ15 በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
  4. በገበያ መጠን
    4.1 በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ፤
    ሀ) ለጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን ከብር 50000 እስከ 75000 መሆን ይኖርበታል፡፡
    ለ) ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን ከብር 100000 እስከ 500000 መሆን ይኖርበታል፡፡
    ሐ) ከኢንተርፕራይዙ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን ውስጥ በኮንስትራክሽን ንዑስ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ቢያንስ ከ30 በላይ፣ በብረት ብረትና እንጨት ንዑስ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ቢያንስ ከ30 በላይ፣ በተቀሩት ዕድገት ተኮር ንዑሳን ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ከ50 በላይ የተገኘው ሽያጭ ከመንግስት የገበያ ትስስር ውጪ መሆን አለበት፡፡
    መ) ኢንተርፕራይዙ ለሌሎች ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በንዑስ ኮንትራት የገበያ ትስስር መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡
    ሠ) ኢንተርፕራይዙ ምርት ለማስተዋወቅ ቢያንስ ሦስት ዓይነት ውጤታማ የማስተዋወቂያ ዘዴዎችን መጠቀም አለበት፡፡
    ረ) ኢንተርፕራይዙ ለደረጃው በተዘጋጀው ኤግዚቢሸንና ባዛር ላይ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የተሳተፈ መሆን ይኖርበታል፡፡
    4.2 በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ፤

    • ሀ) ለጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን እስከ ብር 40000 መሆን ይኖርበታል፡፡
    • ለ) ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዓማታዊ የሽያጭ መጠን ከብር 50001 እስከ 200000 መሆን ይኖርበታል፡፡
    • ሐ) ከኢንተርፕራይዙ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን ውስጥ ኢንተርፕራይዞች ከ60 በላይ የተገኘው ሽያጭ ከመንግስት የገበያ ትስስር ውጪ መሆን ይኖርበታል፡፡
    • መ) ኢንተርፕራይዙ ለሌሎች ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በንዑስ ኮንትራት የገበያ ትስስር የፈጠረ መሆን ይጠበቅበታል፡፡
    • ረ. ኢንተርፕራይዙ ለደረጃው በተዘጋጁ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የተሳተፈ መሆን ይኖርበታል፡፡
    • ሠ) ኢንተርፕራይዙ ምርትና አገልግሎቱን ለማስተዋወቅ ቢያንስ ሦስት ዓይነት የኤሌከትሮኒክስና ፕሪንት ሚዲያ የማስተዋወቂያ ዘዴዎችን መጠቀም ይኖርበታል፡፡

  5. የኢንተርፕራይዙ ምርታማነት
    ሀ) በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለ ኢንተርፕራይዝ ምርታማነት ካለው ሙሉ የማምረት አቅም ቢያንስ 50 በላይ መጠቀም ይኖርበታል፡፡
    ለ) ከኢንተርፕራይዙ አባላት እና ወይም ቋሚ ሰራተኞች ቢያንስ 30 ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የብቃት ማረጋገጫ ማዕከል ያገኙት ሰርተፊኬት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሆኖም ይህ መስፈርት የምግብ ዝግጅት ንዑስ ዘርፍ የሚደራጁትን አይመለከትም፡፡
  6. በተቋማዊ አመራርና አደረጃጀት
    ሀ) ኢንተርፕራይዙ ዘመናዊ የሥራ አመራር ዘይቤ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረ መሆን ይኖርበታል፡፡
    ለ) ኢንተርፕራይዙ ለተሰማራበት የምርት እና ወይም የአገልግሎት ንግድ ሥራ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ ሥራ ላይ ማዋል የሂሳብ መግለጫ /Financial Statement/ ወይም ኦዲት ማስደረግ ይኖርበታል፡፡
    መ) የኢንተርፕራይዙ አባላት እና ሰራተኞችን የሥራ ደህንነት ለመጠበቅ የሥራ ልብስ እና እንደ ንዑስ ዘርፉ ዓይነት የደህንነት መሣሪያዎች የተሟሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
    ሠ) የኢንተርፕራይዙን ሥራ ለማስፋፋት የሚያስችል በፅሁፍ የተዘጋጀ የቢዝነስ ዕቅድ /ፕሮጀክት መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡
    ረ) ከሌሎች ኢንተርፕራይዞች ጋር ስለ ቢዝነስ ሥራ ሃሳብ ለመለዋወጥም ይሁን የጋራ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን የሚያስችል የቢዝነስ ግንኙነት (Business Networking)መፍጠር ይኖርበታል፡፡
  7. በመንግስታዊ ድጋፎች አጠቃቀም
    ሀ) የሚሰጠውን የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተግባር ላይ ያዋለ መሆን ይኖርበታል፡፡
    ለ) የብድር ተጠቃሚ ከሆነ ያልተመለሰ ውዝፍ ብድር የሌለበት መሆን ይኖርበታል፡፡
    ሐ) የማምረቻ ማዕከል ተጠቃሚ ከሆነ የኪራይ ውዝፍ ዕዳ የሌለበት መሆን ይኖርበታል፡፡
  8. በቴክኖሎጂ አጠቃቀም
    ሀ) ኢንተርፕራይዙ ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ለማሻሻል በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት፣ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶችና ሌሎች የቴክኖሎጂ ተቋማት የሚሰራጩ ተፈላጊና አዋጭ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ ለመሆን ቅድመ ዝግጅት ያደረገ መሆን ይኖርበታል፡፡
    ለ) ኢንተርፕራይዙ ከሚጠቀምባቸው የማምረቻ ወይም አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች ውስጥ ቢያንስ 50 በኢነርጂ ብቻ የሚንቀሳቀስ መሆን አለበት፡፡
  9. ግዴታን ስለመወጣት
    ሀ) ኢንተርፕራይዙ የሚጠበቅበትን ዓመታዊ ግብር መክፈል ይኖርበታል፡፡
    ለ) ኢንተርፕራይዙ ዓመታዊ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዕድሳት ማካሄድ ይኖርበታል፡፡
  10. ከታዳጊ ወደ መብቃት ደረጃ የሚሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች ሊያሟሏቸው የሚገቡ መስፈርቶች

    1. በሥራ ዕድል ፈጠራ
      ሀ) በኢንዱስትሪም ሆነ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ የፈጠረው ቋሚ የሥራ ዕድል የኢንተርፕራይዝ አባላቱን ጨምሮ 5 ሰዎችን ያሰማራ መሆን ይኖርበታል፡፡
      ለ) በኢንዱስትሪም ሆነ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ የፈጠረው ቋሚ የሥራ ዕድል የኢንተርፕራይዝ አባላቱን ጨምሮ ከ11 አስከ 30 ሰዎች መሆን ይኖርበታል፡፡
      ሐ) በኢንዱስትሪም ሆነ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ አንሰተኛ ኢንተርፕራይዝ በዓመት ውስጥ በጊዜያዊነት የፈጠረው የሥራ ዕድል ከ10 እስከ 15 ሰዎች መሆን ይኖርበታል፡፡
    2. በሃብት መጠን
      2.1 በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ፤ ሀ) ጠቅላላ የሃብት መጠን የተጣራ ሀብት እና ዕዳን የሚያካትት ሆኖ ለጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ከብር 75001 እስከ 100000 መሆን ይኖርበታል፡፡
      ለ) ጠቅላላ የሃብት መጠን የተጣራ ሀብት እና ዕዳን የሚያካትት ሆኖ ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ከብር 500001 እስከ 1500000 መሆን ይኖርበታል፡፡
      ሐ) ኢንተርፕራይዙ በብድር ካገኘው ገንዘብ ለቋሚ ንብረት ያዋለው 50 እና በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
      2.2 በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ፤
      ሀ) ጠቅላላ የሃብት መጠን የተጣራ ሀብት እና ዕዳን የሚየካትት ሆኖ ለጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ከብር 40001 እስከ ብረ 50000 መሆን ይኖርበታል፡፡
      ለ) ጠቅላላ የሀብት መጠን የተጣራ ሀብት እና ዕዳን የሚያካትት ሆኖ ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ከብር 50001 እስከ ብር 500000 መሆን ይኖርበታል፡፡
      ሐ) ኢንተርፕራይዙ በብድር ካገኘው ገንዘብ ለቋሚ ንብረት የዋለው 20 እና በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
    3. 3 በትርፋማነት
      3.1 በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች
      ሀ) ተመጣጣኝ የትርፍ መጠን በማግኘት በተከታታይ ዓመታት ያስመዘገበ ይኖርበታል፡፡
      ለ) ከተገኘው ትርፍ ሥራውን ለማስፋፋት ያዋለው ኢንቨስትመንት እና ወይመ የቁጠባ መጠን ከተጣራ ሃብት ከ20 በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
      3.2 በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች
      ሀ) ተመጣጣኝ የትርፍ መጠን በማግኘት በተከታታይ ዓመታት ያስመዘገበ መሆን ይኖርበታል፡፡
      ለ) ከተገኘው ትርፍ ሠራውን ለማስፋፋት ያዋለው ኢንቨስትመንት እና ወይም የቁጠባ መጠን ከተጣራ ሃብት ከ20 በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
    4. በገበያ መጠን
      4.1 በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ፤
      ሀ) ለጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን ከብር 75000 እስከ 100000 መሆን ይኖርበታል፡፡
      ለ) ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዐመታዊ የሽያጭ መጠን ከብር 500001 እስከ 1,500000 መሆን ይኖርበታል፡፡
      ሐ) ከኢንተርፕራይዙ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን ውስጥ በኮንስትራክሽን ንዑስ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ቢያንስ ከ35 በላይ፣ በብረታ ብረትና እንጨት ንዑስ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ቢያንስ ከ60 በላይ፣ በተቀሩት ዕድገት ተኮር ንዑሳን ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ከ70 በላይ የተገኘው ሽያጭ ከመንግስት የገበያ ትስስር ውጪ መሆን አለበት፡፡
      መ) ኢንተርፕራይዙ ለሌሎች ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በንዑስ ኮንትራት በዓመት ቢያንስ 4 ጊዜ የገበያ ትስስር የፈጠረ መሆን ይጠበቅበታል፡፡
      ሠ) ኢንተርፕራይዙ ምርት ለማስተዋወቅ ቢያንስ አምስት ዓይነት ውጤታማ የማስተዋወቂያ ዘዴዎችን መጠቀም አለበት፡፡
      ረ) ኢንተርፕራይዙ ለደረጃው በተዘጋጀ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ቢያንስ በዓመት ሶስት ጊዜ የተሳተፈ መሆን ይኖርበታል፡፡
      4.2 በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ፤
      ሀ) ለጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን ከብር 40001 እስከ 50000 መሆን ይኖርበታል፡፡
      ለ) ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን ከብር 200001 እስከ 500000 መሆን ይኖርበታል፡፡
      ሐ) ከኢንተርፕራይዙ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን ውስጥ በኮንስትራክሽን ንዑስ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ቢያንስ ከ35በላይ፣ በብረታ ብረትና እንጨት ንዑስ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ቢያንስ ከ60 በላይ፣ በተቀሩት ዕድገት ተኮር ንዑሳን ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ከ70 በላይ የተገኘው ሽያጭ ከመንግስት የገበያ ትስስር ውጪ መሆን አለበት፡፡
      መ) ኢንተርፕራይዙ ለሌሎች ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በንዑስ ኮንትራት በዓመት ቢያንስ 4 ጊዜ የገበያ ትስስር የፈጠረ መሆን ይጠበቅበታል፡፡
      ሠ) ኢንተርፕራይዙ ምርት ለማስተዋወቅ ቢያንስ አምስት ዓይነት ውጤታማ የማስተዋወቂያ ዘዴዎችን መጠቀም አለበት፡፡
      ረ) ኢንተርፕራይዙ ለደረጃው በተዘጋጀ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ቢያንስ በዓመት ሶስት ጊዜ የተሳተፈ መሆን ይኖርበታል፡፡
    5. የኢንተርፕራይዙ ምርታማነት
      ሀ) በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለ ኢንተርፕራይዝ ምርታማነት ካለው ሙሉ የማምረት አቅም ቢያንሰ 60 በላይ መጠቀም ይኖርበታል፡፡
      ለ) ኢንተርፕራይዙ ለሚያመርታቸው ምርቶችና አገልግሎቶች ዘመናዊ የስራ አመራርን የተከተለ የጥራት ቁጥጥር ሰርዓት የዘረጋ መሆን ይኖርበታል
      ሐ) ለገቢ ወይም ለወጪ ምርቶች የሚውሉ ግብዓቶችን ወይም ገቢ ምርቶችን የሚተካ ወይመ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን ማምረት መቻል ይጠበቅበታል፡፡
      መ) ከኢንተርፕራይዙ አባላት ቢያንስ 75 ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የብቃት ማረጋገጫ ማዕከል ያገኙት ሰርተፊኬት ሊኖራቸው ይገባል፡፡
    6. በተቋማዊ አመራርና አደረጃጀት
      ሀ) ኢንተርፕራይዙ ዘመናዊ የሥራ አመራር ዘይቤ ተግባራዊ ያደረገና ስትራቴጂክ ዕቅድ ሊኖረው ይገባል፡፡
      ለ) ኢንተርፕራይዙ ለተሰማራበት የምርት እና ወይም የአገልግሎት ንግድ ሥራ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ ሥራ ላይ ማዋል እና ዓመታዊ ኦዲት ማስደረግ ይኖርበታል
      ሐ)ኢንተርፕራይዙ አባላትን እና ሰራተኞችን የሥራ ደህንነት ለመጠበቅ የሥራ ልብስ እና እንደ ንዑስ ዘርፉ ዓይነት የደህንነት መሣሪያዎች የተሟሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
      መ) የኢንተርፕራይዙን ሥራ ለማስፋፋት የሚያስችል በፅሁፍ የተዘጋጀ የቢዝነስ ዕቅድ/ፕሮጀክት መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡
      ሠ) ከሌሎች ኢንተርፕራይዞች ጋር ስለ ቢዝነስ ሥራ ሃሳብ ለመለዋወጥም ይሁን የጋራ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን የሚያስችል የቢዝነስ ግንኙነት (Business Networking) መፍጠር ይኖርበታል፡፡
    7. በመንግስታዊ ድጋፎች አጠቃቀም
      ሀ) የሚሰጠውን የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተግባር ላይ አውሎ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣና የአሠራር ተሞክሮውን ለሌሎች ለማስተላለፍ የሚችል፡፡
      ለ) ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም ጋር በትብብርና በኩባንያ ውስጥ ስልጠና የሚሳተፍ፤
      ሐ) ተደጋጋሚ የብድር ተጠቃሚ ሆኖ ያልተመለሰ ውዝፍ ብድር የሌለበት መሆን ይኖርበታል፡፡
      መ)የማምረቻ ማዕከል ተጠቃሚ ከሆነ የኪራይ ውዝፍ ዕዳ የሌለበትና ከማዕከሉ ከመውጣቱ በፊት አስፈላጊውን የፋይናንስና የማምረቻ ቦታ ቅድመ ዘግጅት ያደረገ መሆን ይኖርበታል፡፡
    8. በቴክኖሎጂ አጠቃቀም
      ሀ) ኢንተርፕራይዙ ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ለማሻሻል በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት፣ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶችና ሌሎች የቴክኖሎጂ ተቋማት የሚሰራጩ ተፈላጊና አዋጭ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ መሆን ይኖርበታል፡፡
      ለ) የምርትና አገልግሎት ጥራትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ወቅታዊና የተሻሻለ አሠራር ተጠቃሚ መሆን ይኖርበታል፡፡
      ሐ) ኢንተርፕራይዙ ክሚጠቀምባቸው የማምረቻ ወይም አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች ውስጥ ቢያንስ 75 በኢነርጂ ብቻ የሚንቀሳቀስ መሆን አለበት፡፡
    9. ግዴታን ስለመወጣት
      ሀ) ኢንተርፕራይዙ የሚጠበቅበትን ዓመታዊ የገቢ ግብር መክፈል ይኖርበታል፡፡
      ለ) ኢንተርፕራይዙ ዓመታዊ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዕድሳት ማካሄድ ይኖርበታል፡፡

    ከመብቃት ወደ ታዳጊ መካከለኛ ደረጃ የሚሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች ሊያሟሉዋቸው የሚገቡ ዝርዝር መስፈርቶች

    1. በሥራ ዕድል ፈጠራ
      ሀ) በኢንዱስትሪም ሆነ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ የፈጠረው ቋሚ የሥራ ዕድል የኢንተርፕራይዝ አባላቱን ጨምሮ 30 በላይ ሰዎች መሆን አለበት፡፡
      ለ) በኢንዱስተሪም ሆነ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ በዓመት ውስጥ በጊዜያዊነት የፈጠረው የሥራ ዕድል ከ20 እስከ 30 ሰዎች መሆን ይኖርበታል፡፡
    2. በሃብት መጠን
      2.1 በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ፤
      ሀ) ጠቅላላ የሃብት መጠን የተጣራ ሀብት እና ዕዳን የሚያካትት ከብር 1.5 ሚልዮን በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
      ለ) ኢንተርፕራይዙ በብድር ካገኘው ገንዘብ ለቋሚ ንብረት ያዋለው 70 እና በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
      2.2 በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ፤
      ሀ) ጠቅላላ የሃብት መጠን የተጣራ ሀብት እና ዕዳን የሚያካትት ሆኖ ከብር 500000 በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
      ለ) ኢንተርፕራይዙ በብድር ካገኘው ገንዘብ ለቋሚ ንብረት የዋለው 40 እና በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
    3. በመንግስታዊ ድጋፎች አጠቃቀም
      ሀ) ወደ ኢንዱስትሪ ዞን ለመግባት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ያጠናቀቀ መሆን ይኖርበታል፡፡
      ለ) ከንግድና ልማት ባንኮች ለመበደር የሚያሰችል የብድር ዋስትና ያዘጋጀ መሆን ይኖርበታል፡፡
    4. ግዴታን ስለመወጣት
      ሀ) ኢንተርፕራይዙ የሚጠበቅበትን ዓመታዊ የገቢ ግብር መክፈል ይኖርበታል፡፡
      ለ) ኢንተርፕራይዙ ዓመታዊ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዕድሳት ማካሄድ ይኖርበታል፡፡
      ሐ) አስፈላጊውን የደረጃና የምርት ጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ያገኘ መሆን ይኖርበታል፡፡

    ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር

    1. ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የሚደረገው ሸግግር ዘርፍን፤ካፒታለንና የተፈጠረን የስራ ዕድል መሰረት ያደረገ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት፡-
      ሀ.በኢንዱስትሪ ዘርፍ አባላቱን ጨምሮ ኢንተርፕራይዙ የፈጠረው ቋሚ የስራ ዕድል ከ30 ሰው በላይ፤ጊዜያዊ የስራ ዕድል ከ20 ሰው በላይ ሆኖ ካፒታሉ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሲሆንና በማስራጃ ሲራጋገጥ
      ለ. በአገልግሎት ዘርፍ አባላቱን ጨምሮ ኢንተርፕራይዙ የፈጠረው ቋሚ የስራ ዕድል ከ30 ሰው በላይ፤ጊዜያዊ የስራ ዕድል ከ15 ሰው በላይ ሆኖ ካፒታሉ ከ500000 ሽህ በላይ ሲሆንና በማስራጃ ሲራጋገጥ
    ለበለጠ መረጃ ዕድገት ደረጃ ሽግግር አፈፃፀም ይጫኑ።

ተያያዥ መረጃዎች
© 2023 Yeka woreda 7 Labor E/I/D/Office. Designed by 0912689710