መግቢያ

በሀገራችን ከግብርናው የሥራ ዘርፍ ቀጥሎ አብዛኛው የሰው ኃይል የተሠማራውና ህይወቱን የሚመራው በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የሥራ መስኮች ነው፡፡ በአደጉ እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ተሞክሮ እንዲሚያረጋግጠው ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ለሥራ ፈጣሪነት ልማት እና ለልማታዊ ባለሀብት መፈልፈያ ምንጭ በመሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አገራችን የቀየሰችውን የህዳሴ ጉዞና የተሃድሶ መስመር በማጠናከር ለጀመርነው ፈጣን ልማት ያለንን ሰፊ መሬት፣ ሰፊ የጥሪት ማፍሪያ መስኮች፣ የሰው ጉልበት እንዲሁም ውስን የሆነውን የካፒታል እና የስራ ፈጠራ አቅማችንን ተጠቅመን በሂደት የመካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ባለቤት መሆን ስለሚያስችሉን ነው፡፡

መንግስት ለዘርፉ ልማት በሰጠው ትኩረት በስራ እድል ፈጠራ ላይ በመረባረብ የኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት በማሳደግ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት በከተሞች የተንሰራፋውን ድህነትና ስራ አጥነትን በመቅረፍ የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነትን ለማስፈን የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ ዋነኛው መሳሪያ በመሆኑ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በተደረገ ርብርብ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ ሀገራችን በ2022 ለመድረስ የያዘችውን ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥሩ፣ ለኑሮ አመቺና የነዋሪውን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ተሰልፋ የማየት ግብ ለማሳካት የዘርፉ ሚና በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ እንደ ሀገር እየጨመረ የመጣውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን እንዲሁም የሌሎች ስራ ፈላጊዎችን ቁጥር በተቀናጀ መልኩ በስራ ፈላጊነት በመመዝገብ ባሉት የስራ ዕድል አማራጮች ወደ ስራ ለማስገባት እንዲቻል የድጋፍ አሰጣጥ አግባቡን ወጥ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ትርጓሜ

  1. "ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ" ማለት የኢንተርፕራይዙን ባለቤት፤ የቤተሰብ አባላትና ተቀጣሪ ሰራተኞች ጨምሮ እስከ አምስት ሰዎች ቀጥሮ የሚያሰማራና የጠቅላላ ካፒታሉ መጠን ህንፃን ሳይጨምር በአገልግሎት ዘርፍ ከብር 50000 (ሃምሳ ሺ) ወይም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከብር 100000 (አንድ መቶ ሺ) ያልበለጠ ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡
  2. አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ማለት የኢንተርፕራይዙን ባለቤት፤ የቤተሰብ አባላትና ተቀጣሪ ሰራተኞችን ጨምሮ ከስድስት እስከ ሰላሳ ሰዎች የሚያሰማራና የጠቅላላ ካፒታሉ መጠን ህንፃን ሳይጨምር በአገልግሎት ዘርፍ ከብር 50001 (ሃምሳ ሺህ አንድ) እስከ 500000 (አምስት መቶ ሺህ) ወይም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከብር 100001 (አንድ መቶ ሺህ አንድ) እስከ 1500000 (አንድ ሚልዮን አምስት መቶ ሺ) ያልበለጠ ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡
  3. “ነባር ኢንተርፕራይዝ” ማለት ሕጋዊ ሰውነት ወይም ፈቃድ አግኝተው አንድ ዓመት እና በላይ የሞላቸው ሲሆኑ ሲቋቋሙ የተሟላ ወይም /በከፊል የድጋፍ አገልግሎት ያገኙ ናቸው፡፡
  4. “አዲስ ኢንተርፕራይዝ” ማለት በኢንተርፕራይዞች አደረጃጀት መሠረት ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው ወደ ሥራ ከተሰማሩ አንድ ዓመት ያልሞላቸው ሲሆኑ ሲቋቋሙ የተሟላ ወይም በከፊል የድጋፍ አገልግሎት ያገኙ ናቸው፡፡
  5. “ስራ ፈላጊዎች” ማለት ዕድሜያቸው 18 እስከ 6ዐ ዓመት የሆናቸው፣ የመሥራት ፍላጐትና ችሎታ እያላቸው የራሳቸውን ሥራ በመፍጠርም ሆነ በመቀጠር ቋሚ የሥራ መስክ የሌላቸው፣ ያልተማሩትንና በተለያየ የትምህርት ደረጃ የሚገኙ የሀገሪቱ ዜጐች ናቸው፡፡
  6. "የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ምሩቃን ስራ ፈላጊዎች " ማለት ከመንግስትና ከግል ዩኒቨርሲቲዎች በዲግሪና ከዚያ በላይ፣ ከመንግስትና ከግል ኮሌጆች፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከደረጃ I-V የተመረቁና የመስራት ፍላጎትና ችሎታ እያላቸው የራሳቸውን ሥራ በመፍጠርም ሆነ በመቀጠር ቋሚ የሥራ መስክ የሌላቸው የሀገሪቱ ዜጎች ናቸው፡፡
  7. "የሥራ ዕድል ፈጠራ " ማለት የመስራት አቅም እያላቸው በተለያየ ምክንያት ወደ ስራ ያልገቡ ዜጎችን በጊዜያዊ ወይም በቋሚ የስራ ዘርፎች ማሠማራት ነው፡፡
  8. "ቋሚ የሥራ ዕድል" ማለት የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ ፈጥረው የሚሰሩ ወይም ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ ሊያሰራ በሚችል ድርጅት ውስጥ በቋሚነት ተቀጥረው በፔይሮል ክፍያ በማግኘት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ማለት ነው፡፡
  9. "ጊዜያዊ የሥራ ዕድል" ማለት በጥሪት ማፍሪያ ፕሮጀክቶች የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ በጊዜያዊነት በማቋቋም ከአንድ አመት ላነሰ ጊዜ የሚሰሩ ወይም በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ ከአንድ አመት በታች ለሚሆን ጊዜ በቅጥር የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ማለት ነው፡፡
  10. " የግል ኢንተርፕራይዝ" ማለት አንድ የኢንተርፕራይዝ ባለቤት የሚያቋቁመው እና የንግድ ባለቤት ያለው ሆኖ በንግድ ህጉ የሚገኝ አንዱ አደረጃጀት አይነት ሲሆን የኢንተርፕራይዙ አጠቃላይ እንቅስቃሴ እና ስራዎች በሙሉ ኢንተርፕራይዙ ባቋቋመው አቅምና ፍላጎት የሚወሰን ነው፡፡
  11. "ህብረት ሽርክና ማህበር" ማለት ሕጋዊ ሕልውና ያለው ከንግዱ ማኀበራት ወይም ድርጅቶች ሁሉ ቀላል ቅርጽ ያለው፣ የሸሪኮች አነስተኛ ቁጥር ሁለት ሰው ሲሆን ትልቁ የመስራቾች ቁጥር ገደብ የሌለው እና የአነስተኛ የመነሻ ካፒታሉ በውስጠ ደንቡ ውስጥ አባላቱ ዕጣ (ሼር) ድምር በመነሻ ካፒታልነት በመያዝ የሚመሰረት የንግድ ማህበር አይነት ነው፡፡
  12. "ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር" ማለት በንግድ ህግ አንቀጽ 51ዐ መሠረት ከሁለት አባላት ባላነሰ ከሃምሳ አባላት ባልበለጠ የሚቋቋም ሆኖ የማህበሩ መነሻ ካፒታል ከብር አስራ አምስት ሺ ያላነሰ፣ የማህበሩ አክሲዮን እኩል በሆነ የአክሲዮን ዋጋ የተከፋፈለ ሆኖ የአንድ አክሲዮን ዋጋ ከብር አስር ያላነሰ ሲሆን አባላቱም የተወሰነ ኃላፊነት ያለባቸው ድርጅት/ማህበር ነው፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሆዎች

  1. የሥራ ዕድል ፈጠራው በስራ ፈላጊነት ለተለዩና ለተመዘገቡ ዜጎች ብቻ ነው፣
  2. የወጣቶች፣ የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣
  3. የስራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ አማራጮችን አሟጦ መጠቀም፣
  4. ለሥራ ፈላጊዎች ሁሉ አቀፍ ድጋፍ በመስጠት የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ማድረግ፣
  5. የሚሰጡ ህጋዊነት የማስፈንና መንግስታዊ ድጋፎች በአንድ ማዕከል አገልግሎቶች መስጫ ጣቢያ እንዲያልቁ ማድረግ፣
  6. ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት፣
  7. የስራ ፈላጊዎች ልየታ፣ አመዘጋገብ እና የግንዛቤ ፈጠራ

    የስራ ፈላጊዎች ልየታና ምዝገባ አስፈላጊነት

    ስራ ፈላጊዎችን በጾታ፣ በዕድሜ፣ በትምህርት ደረጃ በመመዝገብ እንደ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲሞግራፊያዊ ገጽታዎች በመረዳት የፌዴራልና የክልል መንግስታት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ለሚቀርጿቸው የልማት ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞችና የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች ዋነኛ ግብዓት ነው፡፡

    ስለሆነም በልየታና በምዝገባ ስራው ላይ ህብረተሰቡንና አደረጃጀቶችን በማሳተፍ ማከናወኑ በተጨባጭ ስራ ፈላጊ የሆኑ ዜጎችን ለመለየት እና ለስራ ዕድል ፈጠራው ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንዲሁም መንግስት በዘርፉ ለሚያደረገው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል መሰረት እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡

    በስራ ፈላጊነት ለመመዝገብ የሚጠየቁ መስፈርቶች

    => የከተማ (የቀበሌ) ነዋሪነት መታወቂያ ያለው/ላት፣
    => የከተማ ነዋሪነት መታወቂያ የሌለው/ላት ከሆነ ቀድሞ ከሚኖርበት/ከምትኖርበት የገጠርም ሆነ የከተማ ቀበሌ አስተዳደር ማንነቱን/ቷን የሚገልጽ መሸኛ የሚያቀርብ/የምታቀርብ፣
    => እድሜው ከ18 እስከ 60 የሆነ/ነች፣
    => የኢትዮጵያ ዜጋ የሆነ/ነች፣
    => ለመስራት ፍላጎትና ችሎታ ያለው/ላት፣
    => በራሱም ሆነ በቅጥር ቋሚ የገቢ ምንጭ/ቋሚ ስራ የሌለው/ላት፣

    የስራ ፈላጊዎች የግንዛቤ ፈጠራ

    የስራ ፈጣሪነት አስተሳሰብ፣ አመለካከትና ክህሎት ስልጠና ከፌደራል ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙት የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲዎች /መምሪያዎች /ጽ/ቤቶች የግንዛቤ ፈጠራ ስራ በስራ ፈላጊነት ለተመዘገቡ ዜጎች በዘርፉ ያሉትን አማራጮች እና ከስራ ፈላጊው ስለሚጠበቅ ዝግጁነት የንቅናቄ መድረክ በማዘጋጀት የስራ ፈላጊ ወላጆችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ አካላት በስራ ዕድል ፈጠራ ስራ ያላቸውን ሚና በማስገንዘብ የጠራ አመለካከት ይዘው እንዲሄዱ የሚደረግ ይሆናል፡፡

    የስራ ፈላጊዎች የአጫጭር የስራ አመራር እና ክህሎት ስልጠና

    በየደረጃው ከሚገኙ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲዎች/ቢሮዎች የጋራ ዕቅድ በማዘጋጀት ለስራ ብቁ ሊያደርጋቸው የሚችሉ አጫጭር የንግድ ስራ አመራር (መሰረታዊ የስራ ፈጣሪነት አመለካከት፣ በአደረጃጀት አማራጮች፣ የንግድ ስራ ዕቅድ አዘገጃጀት፣ መሰረታዊ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ፣ የወጪ ማስላትና ዋጋ ተመን፣ ንብረት አያያዝ፣ ደንበኛ አያያዝ) እና የቴክኒክ ስልጠና አይነቶችን በመለየት በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ከተመዘገቡ ከስራ ፈላጊዎች ዘርፍ ምርጫ ጋር በማጣጣም የሚያመቻች ይሆናል። ለአዲስ ስራ ፈላዎችና አንቀሳቃሾች ገበያ ተኮር አጫጭር የስራ አመራር እና የክህሎት ስልጠና በመስጠት እንዲመዘኑና በሙያ ብቃት ማረጋገጫነት የንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ የሚያገለግል ይሆናል፡፡

    የስራ ዕድል ፈጠራ መንገዶች

    በመደራጀት የሚፈጠር የስራ ዕድል ስራ ፈላጊዎችን ከምዝገባ ጀምሮ የተለያዩ መንግስታዊ ድጋፎችን በማመቻቸት በመረጡት የአደረጃጀት አይነቶች ተደራጅተው በሚሰጣቸው የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እና በሚያወጡት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ መሰረት ወደ ስራ ሲገቡ አዲስ የሚፈጠር ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ነው፡፡ በአደረጃጀት የሚፈጠር የስራ ዕድል የራስ ስራ ፈጠራ ወይም (self employment) ይባላል፡፡

    በቅጥር የሚፈጠር የስራ ዕድል ስራ ፈላጊዎች በቂ ስልጠና ወስደው የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ካገኙ በኋላ ተደራጅተው የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ በማቋቋም የስራ ዕድል መፍጠር ላልቻሉ ስራ ፈላጊዎች በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ በነባር ኢንተርፕራይዞች፣ ከመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ በግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶች፣ በሆቴሎችና በተለያዩ የግል ኢንቨስትመንቶች ላይ በቋሚና በጊዜያዊ ቅጥር የሚፈጠር የስራ ዕድል ነው፡፡ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች በአካባቢያቸው በቅጥር የስራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በመለየት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በማዘጋጀት ለስራ ፈላጊ ዜጎች በቅጥር የስራ ዕድል መፍጠር እንዲችሉ መስራት ይጠበቃል፡፡

    የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አደረጃጀት እና የስራ ዕድል ፈጠራ አማራጮች

    በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለመሰማራት የሚፈልጉ ስራ ፈላጊዎች እና በከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም የአካባቢ ልማት ተጠቃሚ የነበሩና ወደ ዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ የሚሸጋገሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለያዩ የአደረጃጀት አማራጮች መዝግቦ ወደ ሥራ ለማስገባት በተገልጋዮች ፍላጎት መነሻነት በሀገራችን የንግድ ሕግ እና የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ መሠረት በማድረግ አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡

    የንግድ ሕጉ የሚያቅፋቸው የአደረጃጀት ዓይነቶች

    1. በግል የሚቋቋም ኢንተርፕራይዝ፣
    2. የንግድ ማህበራት አደረጃጀት ዓይነቶች ናቸው።

    በግል የሚቋቋም ኢንተርፕራይዝ መስፈርት

    የግል ኢንተርፕራይዝ አንዱ የአደረጃጀት አይነት ሲሆን የኢንተርፕራይዙ አጠቃላይ እንቅስቃሴ እና ስራዎች በሙሉ ኢንተርፕራይዙ ባቋቋመው አቅምና ፍላጎት የሚወሰን ይሆናል፡፡ መስፍርቶቹም፡-

    1. የግል ኢንተርፕራይዝ ምስረታ የማመልከቻ ቅጽ ሞልቶ ማቅረብ የሚችል፤
    2. የስራ አጥ መታወቂያ ካርድ፣
    3. የአመልካቹ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የተነሳው ጉርድ ፎቶ ግራፍ፣
    4. የነዋሪነት የመታወቂያ ካርድ፣
    5. ዕድሜው 18 ዓመት የሞላው መሆን፣
    6. የአዋጭነት የንግድ ስራ እቅድ ማቅረብ፣
    7. የንግድ ስራ አድራሻውን / በመኖሪያ መታወቂያው ላይ ያለውን አድራሻ በሚዘጋጀው የምዝገባ ቅጽ ላይ በመሙላት በፊርማው በማረጋገጥ ማቅረብ የሚችል፣
    8. የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር ሰርተፍኬት፣
    9. የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ለሚያስፈልጋቸው የስራ መስኮች)

    የንግድ ማህበር አደረጃጀት ዓይነቶችና መሥፈርት

    ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ እና ከዘርፉ ልማት ተልዕኮ አንጻር በንግድ ህጉ ካሉት የንግድ ማህበር የአደረጃጀት አማራጮች ውስጥ ስራ ፈላጊዎች ሊደራጁባቸው የሚችሉት በኀብረት ሽርክና ማኀበር እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ብቻ ነው፡፡

    የኀብረት ሽርክና ማኀበር አደረጃጀትና መስፈርት

    የኀብረት ሽርክና ማህበር አደረጃጀት ሕጋዊ ሕልውና ያለው ከንግድ ማኀበራት ወይም ድርጅቶች ሁሉ ቀላል ቅርጽ ያለው አደረጃጀት ነው፡፡ በህብረት ሽርክና አደረጃጀት የሸሪኮች አነስተኛ ቁጥር ሁለት ብቻ ሲሆን የአነስተኛ ካፒታል ጥያቄ ገደብ የለበትም፡፡ ካፒታሉ በውስጠ ደንቡ ውስጥ ቢካተትም ከምዝገባ በፊት መክፈሉ አስፈላጊ አይደለም፡፡ የሙያ ወይም የአገልግሎት መዋጮ የተፈቀደ ነው፡፡ የማቋቋሚያ መስፈርቱም ፡-

    1. በጥቃቅንና አነስተኛ ለመደራጀት ለአንድ ማእከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ የቀረበ ጥያቄ
    2. የማህበሩ አባል ለመሆን የቀረበ የግል ማመልከቻ ከሁለት ጉርድ ፎቶግራፍ ጋር ማቅረብ
    3. የማህበር መመስረቻ ቃለ ጉባኤ ማቅረብ የሚችል
    4. የስራ አጥ መታወቂያ ካርድ፣
    5. የአባላቱ የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ፣
    6. የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ሁለት ፓስፖርት መጠን ያላቸው ጉርድ ፎቶ ግራፍና ከማህበሩ አባላት የተወከለበት የውክልና ማስረጃ ማቅረብ
    7. የፀደቀ የንግድ ስም ስያሜ ማስረጃ፣
    8. የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር ማስረጃ፣
    9. የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ለሚያስፈልጋቸው የስራ መስኮች)
    10. የአዋጭነት የንግድ ስራ እቅድ ማቅረብ፣
    11. በውልና ማስረጃ የጸደቀ የመመስረቻ ጽሑፍ እና የመተዳደሪያ ደንብ፣
    12. የንግድ ስራ አድራሻውን / በመኖሪያ መታወቂያው ላይ ያለውን አድራሻ በሚዘጋጀው የምዝገባ ቅጽ ላይ በመሙላት በፊርማው በማረጋገጥ ማቅረብ የሚችል፣
    ለበለጠ መረጃ የስራ ፈላጊዎች ልየታ፣ አመዘጋገብ እና የግንዛቤ ፈጠራ ይጫኑ።

ተያያዥ መረጃዎች
© 2023 Yeka woreda 7 Labor E/I/D/Office. Designed by 0912689710